BBC Amharic – ኢትዮ-ቴሌኮም-ወዴት-ወዴት

https://www.bbc.com/amharic/44150425 ከአንድ ሳምንት በፊት ኢትዮ ቴሌኮም ለመኖሪያ ቤቶችና ድርጅቶች የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲሰጥ ለሃገር በቀል የግል ድርጅት ፍቃድ ሰጥቻለሁ ብሎ ካሳወቀ በኋላ ዜናው የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። በርካቶች የኢትዮ ቴሌኮም እርምጃ የተሻለ የኢንተርኔት አገልግሎትን ለማግኘት መልካም አጋጣሚ ነው በማለት ተስፋቸውን የገለጹ ሲሆን፤ መንግሥት የግል ኩባንያዎች የቴሌኮም ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ለማድረግ አስቧል ይህም የመጀመሪያው እርምጃ ነው በማለት የሚከራከሩ…

min read

https://www.bbc.com/amharic/44150425

ከአንድ ሳምንት በፊት ኢትዮ ቴሌኮም ለመኖሪያ ቤቶችና ድርጅቶች የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲሰጥ ለሃገር በቀል የግል ድርጅት ፍቃድ ሰጥቻለሁ ብሎ ካሳወቀ በኋላ ዜናው የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

በርካቶች የኢትዮ ቴሌኮም እርምጃ የተሻለ የኢንተርኔት አገልግሎትን ለማግኘት መልካም አጋጣሚ ነው በማለት ተስፋቸውን የገለጹ ሲሆን፤ መንግሥት የግል ኩባንያዎች የቴሌኮም ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ለማድረግ አስቧል ይህም የመጀመሪያው እርምጃ ነው በማለት የሚከራከሩ የዘርፉ ባለሙያዎች አሉ።

ይህ እንዳለ ሆኖ ፍቃድ የተሰጠው ድርጅት ሃገር በቀል አይደለም፣ ባለቤቶቹም ከመንግሥት ጋር ግንኙነት አላቸው የሚሉ ክሶችን ጭምሮ በርካታ አስተያየቶች በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ሲንሸራሸር ቆይቷል።

ከኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርኔት አገልግሎት ለማቅረብ ፍቃድ ከወሰዱት ድርጅቶች መካከል አንዱ አቶ ብሩክ ሞገስ የሚያስተዳድሩት ጂቱጂ (G2G) ግሩፕ ይገኝበታል።

አቶ ብሩክ ጂቱጂ ግሩፕ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሴክተሩን በአራት ከፍሎ እየሰራ የሚገኘ ኩባንያ ነው ሲሉ ስለሚመሩት ድርጅት ያስረዳሉ።

ከአራቱ ምድቦች መካከል አንዱ ጂቱጂ አይቲ ክላሪቲ አንዱ ሲሆን የኢትዮ ቴሌኮም አጋር እና በቅርቡ ለመኖሪያ ቤቶች እና መስሪያ ቤቶች የኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጀ ድርጅት መሆኑንን ያስረዳሉ።

ጂቱጂ ከዚህ ቀደም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የአጭር የጽሁፍ መልዕክትን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ እንደቆየ አቶ ብሩክ ያስታውሳሉ።

የቴሌኮም ዘርፉን ወደ ግል የማዘዋወር የመጀመሪያ እርምጃ?

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ኢትዮ ቴሌኮም የተወሰኑ አገልግሎቶቹን የግል ኩባንያዎች በማሳተፍ እያስፋፋ ይገኛል ይላሉ።

እንደምሳሌም ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢትዮ ቴሌኮም የሲም ካርድ ሽያጩን የግል አከፋፋዮችን በመጠቀም ወደ ገበያ ማቅረቡን የሚያስታውሱት አቶ ዘመዴነህ፤ ይህ የኢትዮ ቴሌኮም ተሞክሮ የሲም ካርድ ሽያጩን በከፍተኛ ደረጃ ከፍ እንዳደረገለት ይናገራሉ።

“አሁንም የግል ኩባንያዎችን በማሳተፍ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማስፋፋት ይህን ፕሮግራም እንዳስጀመረ እንጂ በእኔ ግምት የቴሌኮም ዘርፉን ወደ ግል የማዘዋወር እርምጃ ሆኖ አይታየኝም” ይላሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህር የሆኑት አቶ ጉታ ለገስ በበኩላቸው የቴሌኮም ዘርፉን ወደ ግል ለማዘዋወር ይህ የመጀመሪያው ትንሹ እርምጃ ነው ይላሉ። እንደ አቶ ጉታ ከሆነ የተለያዩ ዘርፎችን ወደ ግል ለማዘዋወር ብዙ ደረጃዎች መታለፍ አለባቸው። ከዚህ አንጻርም የግል ኩባንያዎች የኢንተርኔት አገልግሎቱ እንዲሰጡ ማስቻል የመጀመሪያዋ ትንሿ እርምጃ ነች ሲሉ ያስረዳሉ።

የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ሃላፊ የሆኑት አቶ አብዱራሂም አህመድ በበኩላቸው የቴሌኮም ዘርፉን ወደግል የማዘዋወር እርምጃ ነው የሚለው ”የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። የሞባይል ካርድ እንዲሸጡ ፍቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች፤ የሞባይል ካርዶችን ከቴሌ በብዛት ገዝተው እንደሚቸረችሩት ሁሉ ይህም ድርጅት ከእኛ ይገዛና ለደንበኞቹ ያስተላልፋል እንጂ የፖሊሲ ለውጥ የለም” ሲሉ ተናግረዋል።

የአገልግሎት ጥራት

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ የሆኑት አቶ ተክሊት ሃይላይ የኢንተርኔት አገልግሎት በግል ኩባንያዎች አማካኝነት ለደንበኞች እንዲደርስ ማድረጉ ተደራሽነቱን ከፍ ያደርጋል እንዲሁም የተጠቃሚውን ቁጥር ይጨምራል ባይ ናቸው።

እንደ አይሲቲ ባለሙያው ከሆነ የኢትዮ ቴሌኮም /ኮር ኔትዎርክስ/ ዋና ኔትዎርኮች ብዙ ወጪ የፈሰሰባቸው እና ጥራታቸው አስተማማኝ ነው። አቶ ተክሊት ”የኢትዮ ቴሌኮም የኔትዎርክ ችግር የሚከሰተው ከአክሰስ ኔትወርክ ነው። በየሰፈሩ የሚገኙት የኢትዮ ቴሌኮም ማከፋፈያ ሳጥኖች እስከ ደንበኛው ድረስ ያለው መስመር በተደጋጋሚ ችግር ያጋጥመዋል ይህም በኢንተርኔት ግንኙነት ላይ ችግር ያስከትላል” በማለት ያስረዳሉ።

የጂቱጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ በበኩላቸው በየሰፈሩ ከሚገኙት የኢትዮ ቴሌኮም ማከፋፈያ ሳጥኖች እሰከ ደንበኛው ድረስ ያለው የመስመር ችግርን በመቅረፍ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ያስችለናል ይላሉ።

እንደ አቶ ብሩክ ከሆነ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮ ቴሌኮም ከሚሰጠው የኢንተርኔት ዋጋ ለመኖሪያ ቤቶች ከ10 እሰከ 50 በመቶ እንዲሁም ለንግድ ድርጅቶች ከ5-20 በመቶ ቅናሽ እናደርጋለን ብለዋል።

የድርጅቱ ባለቤትነት

ከዓመታት በፊት ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚንስቴር በስድስት ዓይነት የኢትዮ ቴሌኮም ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ፍቃድ እንደተሰጣቸው፤ ከእነዚህም መካከል አንዱ አሁን የተጀመረው የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሆነ አቶ ብሩክ ይናገራሉ።

የድርጅቱ ባለቤት የማን እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ብሩክ ሲመልሱ ”ድርጅቱ የአክሲዮን ማህበር ነው። የማህበሩን አባላትን ይፋ ማድረግ አልሻም፤ ይሁን እንጂ ከድርጅቱ ባለቤቶች መካከል መግለጫ የሰጠነው እኔ እና ባልደረባዬ ቴዎድሮስ መሃሪ እንገኝበታለን” ብለዋል።

”ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቴ በፊት ኤ ኤንደ ዲ አይቲ ሶሉሽንስ የሚባል ድርጅት በአትላንታ አሜሪካ አቋቁሜ ነበር። ይህን ድርጅት በመያዝ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የተለያዩ ሥራዎችን ለመስራት ስሞክር ተጨማሪ አጋሮች በማግኘቴ ጂቱጂ የሚባል በኢትዮጵያ የተመዘገበ ሃገር በቀል ድርጅት መሰረትን” ሲሉ ይናገራሉ።

የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ሃላፊው አቶ አብዱራሂም ስለ ጂቱጂ ግሩፕ ሲናገሩ ”ይህ ድርጅት ጎልቶ ወጣ እንጂ አጠቃላይ ይህን አገልግሎት እንዲሰጡ ለ8 ድርጅቶች ፍቃድ ሰጥተናል። ዋናው ነገር ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚንስቴር የሚሰጠውን ፍቃድ የሚያገኝ ድርጅት አገልግሎቱን ለመስጠት በዘርፉ ሊሰማራ ይችላል” ብለዋል።